በሁሉም ዘርፍ የሚከናወኑ የልማት ተግባራ

2026-02-05

በሁሉም ዘርፍ የሚከናወኑ የልማት ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የበለጸገ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚገባ ተመላከተ

በሁሉም ዘርፍ የሚከናወኑ የልማት ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የበለጸገ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚገባ ተመላከተ

(ቡታጅራ ጥር 27/2018 )በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ እየተካሔደ ነው

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ እንደገለጹት በሁሉም ዘርፍ የሚከናወኑ የልማት ተግባራትን ለማገዝ በቴክኖሎጂ የበለጸገ ማህበረሰብ መፍጠር ይገባል ብለዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ፣ምርታማነትን በማሳደግ ብሎም ብቁና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ስርዓት እንዲገነባ የሚያስችል ነው ሲሉም ኃላፊው አብራርተዋል።

ክልሉን የሳይንስ፣የቴክኖሎጂ እና የኢኖቬሽን ማዕከል ማድረግ የሚያስችል ስርዓት ተዘርግቶ ወደ ተግባር ስለመገባቱም አቶ ሰላሙ በንግግራቸው አመላክተዋል።

በክልሉ የአካባቢዎችን ጸጋዎች የሚያስተዋውቁና ለተገልጋዩ ህብረተሰብ መረጃ የሚሰጡ 22 ድህረ-ገጾችን ማልማት መቻሉን ጠቁመዋል።

በተቋማት ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ግዢ እና ጥገና ማከናወን ስለመቻሉም ኃላፊው ጠቁመዋል።

በክልሉ ሞዴል የሆነ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተቋቁሞ ስራ እስከሚጀምር ባለው ሂደት በቴክኖሎጂው ዘርፍ ቢሮው የላቀ ድጋፍ አድርጓል ሲሉም አቶ ሰላሙ በአብነት ጠቅሰዋል።

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ (ዶ/ር )ኢኒሼቲቭ የሆነው የ5ሚሊየን ኮደርስ 189 ሺ 738 ወጣቶች እና የመንግስት ሰራተኞች ተመዝግበው የእድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል ያሉት ኃላፊው ከዚህ ውስጥ ከ147ሺ በላይ ዜጎች ስልጠናቸውን በማጠናቀቅ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መውሰዳቸውንም ጠቅሰዋል።

የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ አብይ አላማ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተገኙ መሰረቶችን ማስፋት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

ስትራቴጂው የመረጃ እና የቴክኖሎጂ ሉአላዊነትን መሰረት የሚያደርግ ነው ያሉት ኃላፊው ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ገዢ ሳትሆን ቴክኖሎጂ አምራች እንድትሆን የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀረጸው ስትራቴጂ አሳታፊ ነው ያሉት አቶ ሰላሙ በተለይ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ስኬታማነት የላቀ አበርክቶ እንዳለውም ጠቁመዋል።

የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ተጠቃሚነትን ከማጎልበት ባለፈ የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት እና ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችልም ኃላፊው ተናግረዋል።

በክልሉ በ17 ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ግብ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ሰላሙ ያስታወቁት።

በመድረኩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ ንጉሴ አስረስ (ዶ/ር )ከክልል፣ከፌደራል፣ከዞን እና ከልዩ ወረዳ የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
Back to News